ሱራ አል ከህፍ-ትርጉምና ማብራሪያ



ሱራ አል ከህፍ-ትርጉምና ማብራሪያ
የሙሰሊም ሥነ ምግባር Muslim Manners ®
ሱራ አል ከህፍ (ክፍል አንድ) የወረደበት ምክንያት
የኢስላም ጥሪ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመካ ሙሽሪኮች በጣም ከተገረሙባቸውና ሊዋጡላቸው ካልቻሉ ነጥቦች ውስጥ አንዱ የሙሀመድ ኢብን አብዱላህ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መልእክተኝነት ነበር፡፡ይህን አስመልክቶ የመካዊያን የመጀመሪያ መከራከሪያ ነጥብ ‹የነብይነት ደረጃ ለሠው ልጅ ሊሠጥ የማይችል እጅግ ከፍተኛ የሆነ ደረጃ ነው› የሚል ነበር፡፡ለዚህ ንግግራቸው አላህ የተለያዩ አንቀጾችን በማውረድ መልስ ሰጣቸው፤ስለቀደምት ነብያት ታሪክም አወሳላቸው፡፡ሙሽሪኮች የኢብራሒምንና የኢስማዒልን (ዐ.ሰ) መልእክተኝነት ያውቁና ይቀበሉ ስለነበር በዚህ የመከራከሪያ ነጥባቸው ሊገፉ አልቻሉም፡፡ስለሆነም ‹‹ይህም ቁርኣን ከሁለቱ ከተሞች በታላቅ ሰው ላይ አይወረድም ኖሯልን?አሉ(1)›› ‹አላህ የመካንና የጧኢፍን ታላላቅ ሠዎች ትቶ ይህን የቲም እንዴት ይመርጣል?› እያሉ ጠየቁ፡፡ለዚህም አላህ መልእክቱን የሚያደርግበትን ሥፍራ ይበልጥ አዋቂ መሆኑን(2) ገለጸላቸው፡፡ሙከራቸው ሁሉ ያልተሳካላቸው የመካ ሙሽሪኮች የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መልእክተኝነት በሌላ መልኩ ለማጣራት ፈለጉ፡፡አይሁዶች ስለነብያት ይበልጥ ያውቃሉ ብለው ስላመኑ ስለሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለመጠየቅ አን ነዲር ኢብን አል ሀሪሥንና ዑቅባ ኢብን አቢ ሙዓይጥን መዲና ወዳሉ አይሁዶች ላኳቸው፡፡የአይሁድ ራቢዎች (ቄሶች) ስለሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምና ስለሚናገረው ነገር ከሰሙ በኋላ እንዲህ አሉ፡ ‹‹3 ጥያቄዎችን ጠይቁት፤ከመለሰላችሁ የእውነት ነብይ ነው፤ ያለዚያ ዋሾ ነው፤ማድረግ ያለባችሁን እናንተው ታውቃላችሁ፡፡1. በመጀመሪያ ዘመን የሄዱት ወጣቶች ጉዳያቸው ምን እንደሆነ ጠይቁት፤ ስለነርሱ ድንቅ ወሬ አለ፡፡ 2. ዓለምን ዘዋሪ የሆነና በምድር ጸሀይ መግቢያና መውጫ ስለደረሠው ሰውዬም ጠይቁት፤ 3. ስለሩህም ጠይቁት፤ምንድነች እሷ?››
አን ነዲርና ዑቅባ ጥያቄያቸውን ይዘው ወደመካ ተመለሡ፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጥያቄዎቹ በቀረቡላቸው ጊዜ ከጌታቸው መልስ እንደሚመጣ በማሰብ ‹በሚቀጥለው ቀን መልስ እሰጣችኋለሁ› ብለው ሙሽሪኮቹን መለሱ፡፡ ነገር ግን ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይጠብቁት የነበረው መልስ ሳይመጣ የቀጠሮው ቀን አለፈ፡፡ለተከታታይ 15 ቀናት ምንም አይነት ወሕይ ሳይመጣ ቀረ፡፡በዚህ ጊዜ ሙሽሪኮች ‹ሙሀመድ መልስ ሊሠጠን አልቻለም› እያሉ መሳለቅ ጀመሩ፡፡ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምም በሁኔታው እጅግ አዘኑ፡፡ከ15 ቀናት በኋላ ሱራ አል ከህፍ የሁለቱን ጥያቄዎች መልስ፣ የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ሀዘን የሚያስወግዱ አንቀጸችንና ሌሎች ትምህርቶችን ይዞ ወረደ፡፡የሦስተኛው ጥያቄ መልስ በሱራ አል ኢስራእ አንቀጽ 85 ተሠጠ፡፡ በዚሁ ሱራ ሁሉን አዋቂው አላህ ‹‹ለማንኛውም ነገር እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝም አትበል፡፡አላህ የሻ እንደ ሆነ እሰራዋለሁ (ኢንሻኣለህ)ብትል እንጂ፡፡››(3) ሲል መልእክተኛው (እንዲሁም ማንኛውም ሙስሊም) ወደፊት ሊሠራ ያሰበውን ሲናገር መከተል ያለበትን ሥርዓት አስተምሯል፡፡
እውነትን ቢፈልጉ ኖሮ ይህ ያቀረቡት ጥያቄ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የአላህ መልእክተኛ መሆኑን ሙሽሪኮችን ለማሳመን በቂ ነበር፡፡ይሁን እንጂ በዳዮች ክህደትን እንጂ እንቢ አሉ፡፡
1-ሱራ አል ዙኽሩፍ አንቀጽ 31
2-ሱራ አል አንዓም አንቀጽ 124
3-ሱራ አል ከህፍ አንቀጽ 23-24



ሱራ አል ከህፍ (ክፍል ሁለት)
ከዚህ ቀደም በተለጠፈው ጽሁፍ ምዕራፉ የወረደበትን ምክንያት ተመልክተናል፡፡በዛሬው ጽሁፍ ደግሞ በአላህ ፈቃድ የምዕራፉን የመጀመሪያ አንቀጾች ትርጉምና ማብራሪያ እናያለን፡፡
ሱራው የሚጀምረው ቁርአንን ያለምንም ግድፈት፣ ቀጥተኛና ግልጽ አድርጎ በሙሀመድ ላይ ላወረደው ታላቁ ጌታ ምስጋና በማድረስ ነው፡፡በቀጣይ አንቀጾች አላህ ዐዘ ወጀል ይህን በውስጡ ተቃርኖ የሌለበትን መጽሐፍ ያወረደበትን ምክኒያት እንዲህ ሲል ይነግረናል፡፡
‹‹ቀጥተኛ ሲሆን ከእርሱ ዘንድ የሆነን ብርቱን ቅጣት ሊያስፈራራበት፣ እነዚያንም በጎ ሥራዎችን የሚሠሩትን ምእመናን ለነሱ መልካም ምንዳ ያላቸው መሆኑን ሊያበስርበት፤ (አወረደው)፡፡በእርሱ ውስጥ ዘለዓለም ይኖራሉ፡፡ እነዚያንም «አላህ ልጅን ይዟል» ያሉትን ሊያስፈራራበት (አወረደው)፡፡›› አንቀጽ 2-4
እነዚያ ‹አላህ ልጅ አለው› የሚሉት ራሳቸውም ሆኑ አባቶቻቸው በነገሩ ላይ እውቀት ሳይኖራቸው በአላህ ላይ የቀጠፉት ጸያፍ ንግግር ነው፡፡(1) ጣኦት አምላኪ አረቦች መላኢኮች የአላህ ሴት ልጆች ናቸው ይሉ ነበር፡፡ክርስቲያኖች ኢሣን (ዐ.ሰ) አይሁዶች ደግሞ ኡዘይርን የአላህ ልጅ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ንግግራቸው ከጉድለት ሁሉ ለጠራው አላህ ልጅ መያዝ የማይገባ ባህሪ መሆኑን በዚሁ ሱራ እንዲሁም በሌሎች ሱራዎች ውስጥ በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡ መጥመምን እንጂ መመራትን እንቢ ያሉት ግን በክህደታቸው ላይ ጸኑ፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምም ይህ የህዝባቸው ሁኔታ በጣም ያሳስባቸው ነበር፤ሙሽሪኮቹ ይህን ከአላህ ቁጣ የሚያድናቸውን ጥሪ አለመቀበላቸው ሳያንስ ሙስሊሞችን ማንገላታታቸውና በእርሳቸውም ላይ መሳለቃቸው  እጅግ ያሳዝናቸው ነበር፡፡ አላህ በአንቀጽ 6 ይህን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል፡፡›› ኢብን ከሲር ይህን አንቀጽ ሲያብራሩ ‹‹በዚህ አንቀጽ አላህ መልዕክተኛውን ያጽናናል፤በሱራ አን ነህል አንቀጽ 127 እንዳለው ባለማመናቸው እንዳይተክዝ ይነግረዋል፤ የመልዕክተኛው ኃላፊነት መልዕክቱን ማድረስ ብቻ ስለሆነና መልዕክቱን ባይቀበሉም ራሳቸውን እንጂ ሌላን ማንንም ስለማይጎዱ መልዕክተኛው በሐዘንና በቁጭት ራሱን እንዳያሰቃይ ይነግረዋል›› ብለዋል፡፡
1.ሱራ አል ከህፍ አንቀጽ 5
ሱራ አል ከህፍ (ክፍል ሦስት)
ከረጅም ጊዜ በፊት ንጉሳቸውን በየዓመቱ የሚቀይሩ ህዝቦች የሚኖሩበት ሀገር ነበር፡፡የአንድ ንጉስ የንግስና ጊዜ ሲያበቃ ንጉሱ ውድ ልብሶችና ጌጣጌጦች ተሰጥተውት እንደመሰናበቻ ከተማዋን ይዞራል፡፡ከዚያም ሩቅ ወደሆነ እንደሱ ንግስናቸውን የጨረሱ ሰዎች እንጂ ሌሎች ወደማይኖሩበት ደሴት ብቻውን ይላካል፡፡ታዲያ አንድ ጊዜ ነዋሪዎቹ በዚህ መልኩ ንጉሳቸውን ሸኝተው ሲመለሱ ከባህሩ ዳርቻ ከሰጠመች መርከብ የተረፈ አንድ ሠው ያገኛሉ፡፡አዲስ ንጉስ ስለሚያስፈልጋቸው ይህን ሠው አንስተው ይወስዱታል፡፡ሰውዬውን ንጉሳቸው እንዲሆን ሲጠይቁት ትንሽ ካንገራገረ በኋላ ጥያቄያቸውን ተቀበላቸው፡፡ስለሀገራቸው ህግና ደንብ እንዲሁም በስተመጨረሻ ወደ ደሴቱ ስለመላኩም ነገሩት፡፡  
ከንግስናው ከትንሽ ቀናት ኋላ ንጉሱ ደሴቱን ለመጎብኘት ከሚኒስትሮቹ ጋር ሲሔድ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ከርቀት የሚሰማ የዱር አራዊቶቹ ድምጽና ከዚህ ቀደም የመጡት ንጉሶች ሬሳ ነበር የገጠመው፡፡አንዳች እርምጃ ካልወሰደ በቀኑ መጨረሻ የአውሬ ራት አንደሚሆን የተረዳው ንጉስ ወደሀገሩ ተመልሶ 100 ጠንካራ ሠራተኞችን አሰባሰበ፡፡ከዚያም ወደ ደሴቱ ልኮ አውሬዎቹ እንዲገድሉና ትንሽ ዛፎችን ብቻ አስቀርተው ሌላውን እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡በንጉስነቱ ከሚከፈለው አብዛኛውን ደሴቱ ላይ ማዋል ጀመረ፡፡በየወሩ ሁኔታውን ለመመልከት ንጉሱ ወደ ደሴቷ ሲሄድ የሚዘሩ እህሎችን፣ ጫጩቶችን፣ ፍየሎችንና ሌሎች የቤት እንሰሳትን ይይዝ ነበር፡፡በዚህ መልኩ 9ወራትን ካሳለፈ በኋላ ንጉሱ ዓመቱን ሳይጨርስ አሁኑኑ ወደ ደሴቷ መላክ እንደሚፈልግ ለሚኒስትሮቹ ገለጸላቸው፡፡እነርሱ ግን በሀሳቡ ሳይስማሙ ስለቀሩ ዓመቱን መጨረስ ግድ ሆነ፡፡በዓመቱ መጨረሻ ውድ ልብሶችና ጌጦች ተሰጥተውት ህዝቡን ለመሰናበት መዞር ጀመረ፡፡ለህዝቡ በሚገርም ሁኔታ ወደ ደሴቱ የሚላክ ብቸኛው ደስተኛ ንጉስ ነበር፡፡ ‹‹ካንተ በፊት ለነበሩት ንጉሶች የዚህ ዓይነቱ ቀን እጅግ ያስከፋ ነበር፡፡አንተ እንዴት ደስተኛ ሆንክ?›› ብለው ሠዎች ጠየቁት፡፡‹‹ወደዚህ ዓለም ስትመጣ አንተ እያለቀስክ ሌላው እየሳቀ ነበር፤መኖር ያለብህ ስትሞት አንተ እየሳቅክ ሌሎች እያለቀሱ እንዲሆን አድርገህ ነው” ሲባል አልሰማችሁም?እኔ ህይወቴን ደስተኛ ሆኜ ለመሞት እንዲያስችለኝ አድርጌ ነው የኖርኩት፡፡ሌሎች ንጉሶች አቅማቸውን ሁሉ እዚህ ሀገር ላይ ላለው ህይወት ብቻ ተጠቅመዋል፤እኔ ግን ደሴቱ ላይ ላለ ህይወትም አቅሜን ተጠቅሜበታለሁ፡፡አስፈሪውን ደን ወደሰላማዊ መኖሪያነት ቀይሬያለሁ፤ታዲያ ለምን አዝናለሁ?›› በማለት መለሰላቸው፡፡
በዚች ዓለም ስንኖር ልክ እንደ ሌሎቹ ንጉሶች በዙሪያችን ባለው ቅንጦት ተዘናግተን ወደርሱ መሄዳችን እርግጥ የሆነውንና ዝንተዓለም የምንቆይበትን አኼራ መርሳት የለብንም፡፡የዱንያ ውበት ፈተና እንጂ ሌላ አይደለም፤ የዱንያ ውበት ጠፊ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡አላህ ዐዘ ወጀል ይህን መልእክት ነው በሱራ አል ከህፍ አንቀጽ 7 እና 8 የነገረን፡፡
‹‹እኛ ማንኛቸው ሥራው ያማረ መሆኑን ልንፈትናቸው በምድር ላይ ያለን ሁሉ ለእርሷ ጌጥ አደረግን፤ እኛም በእርሷ ላይ ያለውን (በመጨረሻ) በእርግጥ በቃይ የሌለበት ምልጥ ዐፈር አድራጊዎች ነን፡፡›› ሱራ አል ከህፍ አንቀጽ 7-8
ለማንኛውም ጁመዓ ነውና ሱራ አል ከህፍን መቅራት እንዳንረሳ
image እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፡፡ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡ሱራ አል ሐሽር አንቀጽ 18


No comments:

Post a Comment